Ketar Development Association

የከታር ዴቬሎፕሜንታል አሶሲዬሽን (ከዴአ)

ከታር ዴቬሎፕሜንታል አሶሲዬሽን (ኬዴአ) በ1995 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በሚኖሩ የቀድሞ የበቆጂ ተማሪዎች የተመሠረተ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ሲሆን የሚንቀሳቀሰውም በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአርሲ ዞን በሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ እና በበቆጂ ከተማ አካባቢ ነው። ድርጅቱ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በጂማና በሰሜን ሸዋ አካባቢም በማሕበራዊ ልማት ዙርያ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ችሏል። የከዴአ ዓላማው ሰፊ እንደመሆኑ ከወረዳው አልፎ በአርሲ ዞን ሁሉ ለመሥራት ዕቅድ አለው። አቅም ከፈቀደ በሌሎች ክልሎችም ለመሥራት ራዕይ ሰንቋል።

የከታር ድርጅት ራዕይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከድህነት፣ ከድንቁርናና ከበሽታ ነጻ ሆነው ያልተቋረጠ የሶሺዮ-ኢኮኖሚክ እድገት እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

ይህንንም ራዕይ እውን ለማድረግ ከሚያተኩርባቸው ተግባሮች ጥቂቶቹ፤ የሕዝቡን ጤንነት አጠባበቅ ትምሕርት መስጠት፣ ድኅነትን መቀነስ ላይ የተመሠረቱ ፕሮጀክቶችን መፍጠርና በሥራ ላይ ማዋል፣ መሠረተ ትምሕርትን ማስፋፋት፣ አለመግባባትን በሠላማዊ መንገድና በእርቅ መፍታትን ማስተማር፣ ጎጂ የሆኑ ባሕላዊ እምነቶችን እና ተግባሮችን የማስቆም ዘመቻዎችን ማካሄድ፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በጥንቃቄና በማይባክን መንገድ መጠቀምን ለሕዝቡ ማስተማርና የደን ልማትን ማስፋፋት ናቸው። ከዴአ ከተቋቋመ ጀምሮ ከመንግሥት ጋር በመሥራት የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና በመለወጥ ጥልቅና ሰፊ አወንታዊ ውጤቶችን አስመስዝግቧል። ከዋና ዋናዎቹም በጥቂቱ፤ የግለሰብ መብትና መልካም አስተዳደር፣ የንግድ ወይም ድርጅት ፈጠራ (ኢንተርፕሬነርሽፕ) የአቅም ግንባታና የኤች አይ ቪ መከላከል ዕውቀት ማስፋፋት፣ የደንና የአካባቢው ጥበቃ፣ በውኃ ንጽሕና አጠባበቅና የማህኅበረሰብ ተጠያቂነት ግንዛቤ ማስፋፋት ይገኙበታል። የከዴአ ፕሮግራም በአባሪ 8 ውስጥ ይገኛል። የከዴአ መሥራቾች የነበሩት የቀድሞ የበቆጂ መለስተኛ ትምሕርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ የስም ዝርዝራቸው 16 ተመዝግቧል። የከታር ድርጅትን የሚያስተዳድሩት ስድስት የቦርድ አባላት ናቸው። ዋና መሥሪያ ቤቱም አዲስ አበባ ሆኖ በቆጂ ከተማ ጽ/ቤት አለው።

የከዴአ የወቅቱ የሥራ አመራር ቦርድና ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ

አቶ በቀለ ፀጋዬ (ሊ/መንበር)፣  መ/አ በቀለ ጎንፋ (ም/ሊ/መንበር)፣ ዶ/ር ዲዻ ሚዸቅሶ (አባል)፣  አቶ ሰለሞን በላቸው (አባል)፣  አቶ አረጋ ተስፋዬ (አባል)፣  ኮ/ር ኡርጋ ዲለሌቻ (ሥራ አስኪያጅና የቦርዱ ጸሐፊ) ናቸው።

በከዴአ እስካሁን የተገኙ ስኬቶች

·       በበርካታ ሁኔታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምሕርትና ሥልጠና ተሰጥቶ ጠያቂ ሕብረተሰብ በመፍጠር በኩል ስኬት አስገኝቷል፤

·       የገበሬ ማሕበራትን ማደራጅትና ማጠናከር በመቻሉ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፤

·       የእርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻልና ጥሩ ዋጋ የሚያወጡ ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለአርሶ አደሩ  አመራሮች ከግብርና ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ሥልጠና ተሰጥቷል፤

·       የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅና አስተዳደር አስመልክቶ ሥልጠና ተሰጥቷል፤

·       ጎጂ ባሕላዊ ልምዶችን ለማስቀረት ከሕብረተሰቡ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል (እነዚህ ልምዶችና ልማዶች ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ያለአቻ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ግግ ማስቧጠጥ፣ አባወራ ሲሞት ያለው አንድ በሬ ተሸጦ ወይም ታርዶ ለተዝካር ማዋል፣ ለጥሎሽና ለኒካ የሚሰጥ ከአቅም በላይ የሆነ ሰጦታ የመሳሰሉት)፤

·       በእምነት ሳቢያ በጥንቆላና በመሳሰሉት ሕብረተሰቡን ከሚያጭበረብሩ ግለሰቦች እንዲጠነቀቁ ማስተማር ተችሏል፤

·       ለወጣት ሥራ አጥ የሥራ ፈጠራ (አንተርፐሬኔርሺፕ) ሥልጠና በመሰጠቱ ብዙዎቹ ተጠቃሚ ሆነዋል፤

·       በርካታ ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢ አርሶ አደሮችና ት/ቤቶች ለማከፋፈል በመቻሉ ተጠቃሚ ሆነዋል፤

·       በኤች አይ ቪ ዙሪያ ጥሩ ግንዛቤ ማስጨበጥ በመቻሉ የቫይረሱ ስርጭት ለመቀነስ ተችሏል፤

·       ሕብረተሰቡ የመብት ጠያቂነትንና የመንግሥትን ተጠያቂነት አስመልክቶ ሰፊ ግንዛቤ በመሰጠቱ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለመጠየቅ የሚያስችለው ቁመና አግኝቷል፤

·       የበቆጂ ት/ቤቶችን አቅም ለማሳደግ ይቻል ዘንድ በርካታ አጋዥ መጻሕፍትንና ያገለገሉ ኮምፒውተሮችን በማበርከት ተማሪዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል፤

·       በበቆጂ ከተማ አንድ ጽ/ቤት ለመክፈት በመቻሉ የመስክ ሥራውን በቅርበት ለመከታተል ከመቻሉም በላይ የአካባቢ ልጆችን መቅጠር ተችሏል፤

·       አቅመ ደካማ ለሆኑት 10 የበቆጂ ነዋሪዎች  ቤታቸውን ከማደስም በላይ መሠረታዊ የፍጆታ አቅርቦትም አድርጎላቸዋል፤

·       ከዴአ ከመንግሥት ጋር በፈጠረው መልካም ግንኙነት በሚያደርጋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ጥሩ ትብብር ያገኛል።